1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እንወያይ፤ የ12 ኛ ክፍል ተማሪዎች ወደቁ የተባሉበት አሳሳቢዉ ዉጤትና አንደምታዉ

እሑድ፣ ጥቅምት 11 2016

ከ 800 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች መዉደቃቸዉ ብቻ ሳይሆን፤ በችግር ያስተማሩ ወላጆች ብሎም በህብረተሰቡ ላይ የሚፈጥረዉ ጫና ቀላል አለመሆኑ ነዉ። የችግሩ መንስኤ ምንድነው? የትምህርት ስርዓት ዉድቀት? ጥቂት ተማሪዎች ብቻ ለከፍተኛ ተቋማት በቁ፤ ብዙኃኑ ግን ወድቋል፤ የተባለለበትን ፈተና የወደቀዉ ማነዉ? እንዴት ትገመግሙታላችሁ? ጻፉልን!

https://p.dw.com/p/4Xroi
ብርኃኑ ነጋ፤ የኢትዮጵያ ትምህርት ሚንስትር
ብርኃኑ ነጋ፤ የኢትዮጵያ ትምህርት ሚንስትር ምስል Education Ministry of Ethiopia

እንወያይ፤ በተስፋ የተሞሉ ተማሪዎች መዉደቃቸዉ የተሰማበት ዜና፤ በኑሮ ዉድነት በቀዉስ ብሎም ከጦርነት ወጥታ ወደ ሌላ ጦርነት ለገባችዉ ሃገር ኢትዮጵያ ሌላ እራስ ምታት ነዉ። ሃላፊነቱን ማን ይዉሰድ?

በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ከወሰዱ 845 ሺህ ገደማ ተማሪዎች መካከል፤ ወደ ዩኒቨርስቲ መግቢያ የማለፊያ ነጥብ ያመጡት ተፈታኞች ብዛት 27,267 ተማሪዎች መሆናቸውን ሰሞኑን ትምህርት ምንስቴር ገልጿል። ይህም ከጠቅላላው ተፈታኝ ተማሪዎች ማለፍ የቻሉት  3.2 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው።ይህ ውጤት እጅግ መነጋገሪያ ከመሆኑ ባሻገር በብዙዎች ዘንድም ድንጋጤን አጭሯል።

ትምህርት ሚኒስቴሩ የተፈታኞች ዉጤት ለህዝብ ይፋ ሲያደርጉ፤ ባለፈው ዓመት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር “በጣም ከፍተኛ የሚባል መሰረታዊ ለውጥ የለም” ብለዋል። ይሁን እና በኢትዮጵያ በርካታ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ማለፍ ያልቻሉት ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ነው። ይኸዉም ትምህርት  ሚኒስቴር ኩረጃን ለማስቆም ሲል ተፈታኞችን በተለያዩ ዩንቨርስቲዎች መላክ ከጀመረ በኋላ መሆኑ ነዉ። 

 ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ 16,451 የማታ ተማሪዎች መካከል፤ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያመጡት 12ቱ ብቻ መሆናቸዉ፤ ከሁሉም በላይ በኢትዮጵያ ዉስጥ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል ከ 1000 ሺህ በላይ የሚሆኑት  ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ አለማሳለፋቸዉ እንደ ሃገር ወዴት እየሄድን ነዉ የሚል ጥያቄ የሚያነሱ በርካቶች ናቸው።ውይይት፦ አከራካሪው የትምህርት እና ስልጠና ፍኖተ ካርታ

ከ 800 ሺህ በላይ የሚሆኑ የ 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናውን መዉደቃቸዉ ብቻ ሳይሆን፤ በችግር ያስተማሩ ወላጆች ብሎም በህብረተሰቡ ላይ የሚፈጥረዉ ጫና ቀላል የሚባል አይደለም።  አሳሳቢዉ የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ዉድቀት ፤ የችግሩ መነሻ ምንድነው? መፍትሄዉስ? ይህ ጥቂት ተማሪዎች ብቻ ለከፍተኛ ተቋማት በቁ ብዙኃኑ ግን ወድቋል፤ የተባለለበት ፈተና ዉጤት የወደቀዉ ማነዉ?  ዉጤቱን እንዴት አያችሁት? እንዴትስ ትገመግሙታላችሁ? 

--ብዙ ጊዜ፣ ገንዘብ እና ጉልበት ባክኖ ለዓመታት የተደከመባቸው ተማሪዎች   3,2 በመቶ ብቻ አለፉ፤  97 % ደግሞ ወደቀ ማለት ለአንድ የትምህርት ስርዓት ምን ማለት ነዉ?  የወደቀዉ ማን ነዉ ይላሉ? የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የመልቀቅያ ፈተና ዉጤት እንዴት ይገመገማል? የስራ እድል እቅድ ለዩኒቨርስቲ ተመራቂዎች 

--ችግሩ ምንድን ነዉ?  እንዴት እዚህ ደረስን?  ትዉልድ እየገደልን አይደለም ወይ ? ኪሳራ አይደለም ወይ? 

--የፈተና ዉጤቱ የሃገሪቱ የትምህርት ስርዓት የተበላሸ መሆኑን የሚያሳይ ነው። በቂ ነጥብ የላችሁም የተባሉት ተማሪዎችም፤ የሀገሪቱ ግራ የተጋባ የትምህርት ስርዓት ሰለባ ናቸው፤ የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም ። በዚህ ይስማማሉ? 

--ዉጤቱስ እንደ ሀገር የት ያደርሰናል? በትምህርት ጥራት ላይ እየተሰራ መሆኑ ተደጋግሞ   ሲነገር ነበር። ለምንድን ነዉ ለውጥ ያልታየዉ?  ፈተናውን ያላለፉት ልጆች በቀጣይ ምን አይነት መፍትሄ  ይኖራቸዉ ይሆን? የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል

--የችግሩ መንስኤ ከዩኒቨርሲቲዎች የመቀብል  አቅም  እና ፍላጎት? ከመንግሥት በጀት ውይስ ሌላ አጀንዳ ይኖረው ይሆን? የሚሉ አሉ ይህስ እንዴት ይታያል። ይህ አስተያየት የመጣዉ ዩንቨርስቲዎች የራሳቸዉን በጀት እንዲችሉ ይደረጋል የሚል ዜናዎች መዉጣታቸዉን ተከትሎ ነዉ። 

--በ16 እስከ 20 ዓመት እድሜ ክልል የሚገኙ በተስፋ የተሞሉ በርካታ ተማሪዎች ፈተና መዉደቃቸዉ የተሰማበት ዜና፤ መቼም ከጦርነት ወጥታ ወደ ሌላ ጦርነት ለገባችዉ ሃገር፤ በመፈናቀል፤ በድርቅ፤ በገቢ ችግር እና በሌሎች ቀውሶች ሳቢያ ትምህርታቸዉን ያቋርጡ፤ ተፈናቅለዉ የሚገኙ በሚዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናት ላሉባት ሃገር ሌላ እራስ ምታት ነዉ ።  ሃላፊነቱን ማን ይዉሰድ? ችግሩ ግን ከማን ይሆን? ከተማሪዎች፣ ከትምህቱ አስጣጥ እና ከትምህርት ካሪኩለም፤ ወይስ ከመምህራን፤ ወይስ ከፈትናው? አልያም ከአስተራረም?

የODA ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በኦሮሚያ
የODA ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በኦሮሚያምስል Seyoum Getu/DW

--ወጣቱ ትውልድ በሀገሩ ተስፋ ቆርጦ ወደ ስድት አልያም ወደ ሌላ ጥፋት ተሰማርቶ ለሀገርም ለቤተሰብም ችግር አንዳይሆን መንግሥት እና ማህበረስቡ አጥብቆ ሊያስብበት ግድ ይላል ሲሉ ብዙዎች አስተያየታቸዉን ይሰጣሉ። መፍትሄዉ ምን ይሆን?  ይህ ችግር እንዲቀረፍ የትምህርት ስርዓቱ እንዲሻሻል፤ ማን ምን ማድረግ ምንስ መደረግ ይኖርበታል ?አንድ ሚሊየን የሚጠጋ ተማሪ ለፈተና ተቀምጦ 50 ሺህ የሚሞላ እንኳን ያላለፈበት የ 2015 ሀገር አቀፍ ፈተና

በዚህ ዉይይት ላይ እንዲሳተፉ የጋበዝናቸዉ፤

ዶ/ር እዮብ አየነው፤  በኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት ልማት ዘርፍ የግል ከፍተኛ ተቋማት አገልግሎት ኃላፊ

ተባባሪ ፕሮፌሰር መስፍን ሞላ፤  በዲላ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት እና ስነ-ባህሪ ተቋም ዲን 

ተባባሪ ፕሮፌሰር ሮብሰን ማርጎ፤  በአርሲ ዩንቨርስቲ የስርዓተ የትምህርት ክፍል መምህር እና  የኢትዮጵያ ወጣቶች ልዩ ተሰጥኦ ግንባታ ማህበር መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ፤ እንዲሁም

ዶ/ር በፍቃዱ ዘለቀ፤ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አባል ናቸዉ።

ሙሉዉን ዉይይት የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን! እናንተም አስተያየቶቻችሁን ጻፉልን!

አዜብ ታደሰ