1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጋምቤላ ክልል በላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች መበራከት

ሐሙስ፣ መጋቢት 19 2016

ከጋምቤላ ከተማ ወደ ኑዌር ዞን ይንቀሳቀስ ነበር በተባለው ተሽከርካሪ ላይ በደረሰው ጥቃት የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአካባቢው ነዋሪዎች ለዶይቼቨለ ተናግረዋል። ጥቃቱ የደረሰው ትናንት ረቡዕ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ኢታንግ ልዩ ወረዳ አካባቢ ነው። ጥቃቱን ያደረሱ ሐይሎች ግን አለመያዛቸውን ነው ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች የገለጹት።

https://p.dw.com/p/4eECh
ፎቶ ከማኅደር፤ የጋምቤላ ከተማ
በጋምቤላ ክልል የተለያዩ ቦታዎች በተደጋጋሚ በሚደርሱ ጥቃቶች በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ እንደሚገኝ ያነጋርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። ፎቶ ከማኅደር፤ የጋምቤላ ከተማ ምስል Negassa Desalegn/DW

በጋምቤላ ክልል በላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች መበራከት

በጥቃቱ የአምስት ሰዎችይወት አልፏል

በጋምቤላ ክልል የተለያዩ ቦታዎች በተደጋጋሚ በሚደርሱ ጥቃቶች በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ እንደሚገኝ ያነጋርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። ከክልሉ ርዕሰ ከተማ ወደ ኑዌር ዞን ያቀና በነበረ አንድ ተሸከርካሪ ላይ ትናንት አራት ሰዓት ገደማ በደረሰው ጥቃት የአምስት ሰው ሕይወት ማለፉን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ ለዶቸቨለ አመልክተዋል። በጥቃቱ በርካቶች ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው አክልዋል። በአካባቢው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት የሚፈጸሙ አካላት መበራከታቸውን የሚገልጹት ነዋሪው በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱ ቡድኖችን መንግሥት ለሕግ እንዲያቀርብም ጠይቀዋል።

በህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ በደረሰው ጥቃት የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የነገሩን ሌላው የአካባቢው ነዋሪም በደረሰው ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መቁሰላቸውን ተናግረዋል። ጥቃት አድረሰዋል የተባሉ ሀይሎች ጭምብል ለብሰው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ነው ነዋሪው የገለጹት። በአካባቢው እዚህም እዚያም የሚከሰቱ ጥቃቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መበራከታቸውን እና የጸጥታው ሁኔታ አስጊ መሆኑን ነዋሪው አክለዋል።

ፎቶ ከማኅደር፤ ጋምቤላ ክልል ባሮ ወንዝ
በጋምቤላ ክልል በህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ በደረሰው ጥቃት የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን፤ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎችም መቁሰላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።ፎቶ ከማኅደር፤ ጋምቤላ ክልል ባሮ ወንዝምስል privat

ኢሰመኮ በጉዳዩ ላይ መረጃ እያሰባሰበ መሆኑ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የጋምቤላ ክልል ቅርንጫፍ በበኩሉ ጉዳዮችን እየተከታተሉ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የኮሚሽኑ ጋምቤላ ቅርንጫፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ አበል አዳነ ኮሚሽኑ በክልሉ ላይ ያተኮረ ዘገባ በየካቲት ወር 2016 ዓ.ም ካወጣ በኃላም በክልሉ የተለያዩ ቦታ ጥቃቶች መድረሳቸውን ተደጋጋሚ ጥቆማዎች እንደደረሷቸው አመልክተዋል። ሰሞኑን የደረሱ ጥቃቶችን አስመልክቶም ተቋማቸው መረጃዎችን እያሰባሰበና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በጋምቤላ የደረሱት ተደጋጋሚ ጥቃቶችን አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጡን ለክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ኃላፊ  ስልክ ብንደውልም አልተነሳም። በጋምቤላ ክልል አቦቦ ወረዳም ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2016 የታጠቁ ሰዎች አድርሰዋል በተባለው ጥቃት እንደዚሁ የሰዎች ሕይወት ማለፉን ዘግበናል።

ነጋሳ ደሳለኝ 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ