1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰብአዊ መብት በኢትዮጵያ፣

ዓርብ፣ ጥር 8 2001

በኢትዮጵያ፣ የ 1997 ቱን ምርጫ ተከትሎ፣ በተቃውሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ ከተወሰደው የማዋከብ፣ ብሎም በመጨረሻ መሪዎቹ ተይዘው ከታሠሩበት እርምጃ ወዲህ ፣ በቅርቡ፣ የዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ ጆሮ ዳግመኛ የሳበ፣ አሳሳቢ የሰብአዊ መብት ይዞታ አለ በማለት የውጭ ታዛቢዎች በመናገር ላይ ናቸው።

https://p.dw.com/p/Ga5I
የጀርመን መራኂተ-መንግሥት ወ/ሮ አንጌላ ሜርክል፣ በጥቅምት ወር 2000 ዓ ም፣ አዲስ አበባ ውስጥ፣ ከኢትዮጵያ ጠ/ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጋር በቤተ-መንግሥት ሲወያዩ፣ምስል picture-alliance/dpa

ከእነዚህም አንዱ፣ በጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የሰብአዊ መብት ፖለቲካ ተጠሪና የሰብአዊ እርዳታ ጉዳይ ተመልካች Günter Nooke ናቸው። በታንዛንያና በኢትዮጵያ የአንድ ሳምንት ጉብኝት አድርገው የተመለሱትን እኒሁን ጀርመናዊው የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ተመልካች ባለሥልጣን ፣ የዶይቸ ቨለ ባልደረባ ሉድገር ሻዶምስኪ አነጋግሯቸዋል፣ ተክሌ የኋላ፣ የጭውውቱን ፍሬ-ሐሳብ እንደሚከተለው አቅርቦታል።

ሃይማኖትና ጎሣ በማይለያያቸው ኢትዮጵያውያን መካከል ዕርቀ-ሰላም እንዲወርድ ፣ ፍቅርና ሰላም አንዲነግሡ፣ በማዜም የታወቀው ዝናኛ ወጣት የኪነት ሰው፣ ቴዎድሮስ ካሣሁን፣ በፍርደ ገምድልነት ነው የታሠረ የሚሉ በተለይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ በነጻ እንዲለቀቅ ድምጻቸውን ሲያስተጋቡ ከቆዩ በኋላ፣ በቅርቡ የአንድነት ለዴሞክራሲና ፍትኅ ፓርቲ ሊቀመንበር የወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሣ መደገም ይበልጥ ቁጣቸው እንዲያይል አድርጎ ከሰሞኑ በብዙ ምዕራባውያን ከተሞች ለተቃውሞ ሰልፍ እንዲወጡ ከገፋፏቸው ምክንያቶች በዋነኛነት ተጠቃሾች ናቸው።

ሉድገር ሻዳምስኪ እንዳለው፣ በኢትዮጵያ ባለፉት ሳምንታት የፖለቲካው አየር ይበልጥ ነው የተባላሸው። የተቃውሞ ወገን የፖለቲካ መሪ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ አዲስ አበባ ውስጥ በአሰከፊው ቃሊቲ ወህኒ ቤት ተመልሰው ታሥረዋል። ወት ብርቱካን ዕድሜ ይፍታኅ እንዳይታሠሩም ያሠጋል። የ 35 ዓመቷን ወ/ት ብርቱካንን መንግሥት የተበቀላቸው(ይዞ ያሠራቸው፣) በአውሮፓ በተዘዋወሩበት ባለፈው ጉብኝታቸው፣ በሰብአዊ መብት አጠባበቅ ረገድ መንግሥት ጉድለት ይታይበታል ብለው በንግግራቸው ላይ በመንቀፋቸው ነው። የ ወ/ት ብርቱካንን ጉዳይ አንስተው፣ኢትዮጵያ ውስጥ ከውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ጋር የተወያዩት ጉዑንተር ኖከ እንደሚሉት እኒህን የተቃውሞ የፖለቲካ ድርጅት መሪ በማሠር፣ መንግሥት በሚመጣው ዓመት የሚካሄደውን አጠቃላይ ምርጫ በተመለከተ፣ ከወዲሁ የተቺዎችን አፍ ለመዝጋት ነው ይህን የሚያደርገው።

«ፍጹም ግልጽ ነው። እዚህ ላይ ፣እኔ እንደሚገባኝ በ 2002 ዓ ም (2010) ለሚካሄደው ምርጫ የተቃውሞው ወገን የሚያደርገውን ዝግጅት በሰፊው ለማሠናከል ነው እንቅሥቃሴ የተያዘው። እናም፣ እንደሚመሰለኝ ፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተጨማሪ ተቀውሞዎች ያስፈልጋሉ። ጀርመንና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ወ/ት ብርቱካን በነጻ እንዲለቀቁ መጠየቃቸው ትክክል ነው ። በተጨማሪም በተነጋገርኩበት ወቅት፣ ቢያንስ የጉዳዩ ሂደት ግልጽነት እንዲኖረው፣ ከአውሮፓው ኅብረት አባል አገሮች አምባሳደሮች መካከል አንዱ ፣ወ/ት ብርቱካንን ለመጠየቅ ፈቃድ ያግኝ ብያለሁ። »

በቅርቡ፣ አንድ እጅግ አከራካሪ የሆነ፣ የመንግሥታት ያልሆኑ የውጭ ድርጅቶች ምዝገባና መተዳዳሪያ ህግ እንዲጸድቅ ሲደረግ፣ የዴሞክራሲ ግንባታን ሂደትና የሰብአዊ መብትን ይዞታ በእጅጉ የሚቀይድ ነው። በመሆኑም ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ አቤት ነው ያለው።

«ዴሞክራቲክ ያልሆኑ መንግሥታት፣ የሚገዙትን አገር ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ለመቆጣጠር ፣ እንዲህ ዓይነት የመንግሥታት ያልሆኑ ድርጅቶች መተዳደሪያ ደንብን ማውጣት ይወዳሉ። ይህን የሚያደረጉት በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ገንዘብ ወይም በ NGO ዎች በሚሠሩ ባለሙያዎች አማካኝነት የሆነ ውስጣዊ የፖለቲካ ክርክር እንዳይነሣ ለማድረግ ነው። ይህ እኔ እንደምገነዘበው፣ መንግሥት ካለው ግብ እጅግ ርቆ የሄደ አሠራር ነው። እርግጥ ነው በአንድ ሀገር መረጋጋት ምንጊዜም ዋጋ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ነገር ግን ሲቭሉ ኅብረተሰብ በትጋት ሳይሳተፍበት፣ የመንግሥት ያልሆኑ ድርጅቶችም ነጻ ሆነው መሥራት ሳይችሉ ዘላቂነት ያለው መረጋጋት ሊሠፍን አይችልም። ኢትዮጵያ ውስጥ፣ በተጨማሪ ሰብአዊ እርዳታና የልማት ተራድዖ(ዐቢይ ግምት ስለሚሰጣቸው)በእርግጥ ደንቡ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ፣ ሰብአዊ እርዳታና የልማት ተራድዖ ቀጥ የሚሉበት ሁኔታ ሊከሠት ይችላል።»

ጉዑንተር ኖከ፣ አሁን እንደሚያስገነዝቡት፣ ገንዘብ ሰጪ አገሮች የገንዘብ እርዳታ ሲንበሸበሽላት በነበረችው ሀገር ላይ(በኢትዮጵያ ላይ )ተጨማሪ እገዳ የማድረግ ኀላፊነት ሊሰማቸው ይችላል። ቀጥተኛው የበጀት መደጎሚያ እርዳታ የ 1997 ዓ ም ምርጫ ከተጭበረበረ በኋላ መቋረጡ ይታወሳል።

«እንደሚመስለኝ ፣ የልማት ተራድዖውና የልማት ገንዘብ የሚቀናጅበት ሁኔታ ያላንዳች ሳንክ እንዲሁ ሊቀጥል አይችልም። የአዲሱ ትልቅ የተቃውሞ ፓርቲ መሪ ወ/ት ብርቱካን እንደታሠሩ፣ አዲሱ፣ የመንግሥት ያልሆኑ ድርጅቶች መመዝገቢያና መተዳደሪያ ደንብም፣ መዘዝ ይኖረዋል እንጂ እንዲሁ፣ ሁሉ ባለበት ሲቀጥል፣ በዝምታ አይታለፍም።»