1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የንግዱ ማህበረሰብ እና የመንግስት ግንኙነት መድረክ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 19 2015

የሕጋዊ ምንዛሬ እና ጥቁር ገበያ ልዩነት እጅግ እየሰፋ መምጣት ለሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ኪስ ማደለቢያ ሲሆን ለሕጋዊ ነጋዴዎች ፈተና ሆኗል የሚለው ምሬት ከተነሱት ጥያቄ አዘል አስተያየቶች መካከል ይጠቀሳሉ። የመብራት መቆራረጥና የኢኮኖሚው በደላሎች መዘወር ከተነሱ ሌሎች ጥያቄዎች ናቸው፡፡

https://p.dw.com/p/4UQd4
Äthiopien Handel und Tourismus vor Herausforderungen | Sitzung Regierung und Privatsektor
ምስል Seyoum Getu/DW

የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ ክፉኛ የፈተኑት ሕገ-ወጥ ንግድና ድላለ

አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው አገር አቀፍ የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ የጋራ የምክክር መድረክ በተደረገው ውይይት ከሕገ-ወጥ ምንዛሪ ጀምሮ በርካታ ተግዳሮቶች እንደሚገጥሟቸውም የንግዱ ማህበረሰብ አንስቷል፡፡ መንግስት በፊናው የንግድ ማህበረሰቡ በኢኮኖሚው ፍትሃዊነትን ለማስፈን ጉልህ ድርሻ እንዳለው ያነሳል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና ከፓን አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው አገር አቀፍ የመንግስት እና የግል ዘርፍ የምክክር መድረክ አበይት አገራዊ ጉዳይ ናቸው በተባሉ የአግሮ ፕሮሴሲንግ፣ ቱሪዝም እና ኢ-ኮሜርስ (ዲጂታል ግብይት) ዘርፎች ጥናቶች ቀርበው ተመክሮባቸዋል፡፡ የውይይቱ ዓለማም ቁልፍ የተባሉ እነዚህን i,ኢኮኖሚ ዘርፎች ማነቃቃት ነው፡፡ ባለፉት ሶስት ዓመታት ገደማ በአገሪቱ በተከሰቱ ችግሮች ምክንያት የግል እና መንግስት ዘርፉ ተቀራርበው የመወያየት ልምድ ተቀዛቅዞ እንደነበር የገለጹት የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው፤ አሁን መልሶ የጀመረው ምክክሩ ችግሮችን በሰከነ መልኩ የመፍታት አቅም እንደሚፈጥር እምነታቸውን አመልክተዋል፡፡

Äthiopien Handel und Tourismus vor Herausforderungen | Sitzung Regierung und Privatsektor
ምስል Seyoum Getu/DW

መሰል የውይይት መድረክ የፖሊሲ ማሻሻያ ግብዓቶችም ጭምር ሃሳቦች የሚመነጩበት ነው ያሉት ደግሞ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተሻለ በልሁ ናቸው፡፡ “የምክክር መድረኩ በቅን ልቦና ከመከርንበት በመንግስትና በግሉ ዘርፍ የጋራ መፍትሄ የማፈላለግን ባህል በእጅጉ የሚያጎለብት ነው፡፡ ውይይቱም ፍሬያማና መፍትሄ ተኮር ይሆናል፡፡”

ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጡ የንግዱ ማህበረሰብም አማሮናል ያሉዋቸውን በንግዱዓለም እና በአምራችነት ሂደት ውስጥ ስለሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ለሚመለከተው የመንግስት አካላት አንስተዋል፡፡ የሕጋዊ ምንዛሬ እና ጥቁር ገበያ ልዩነት እጅግ እየሰፋ መምጣት ለሕገወጥ ነጋዴዎች ኪስ ማደለቢያ ሲሆን ለህጋዊ ነጋዴዎች ፈተና ሆኗል የሚለው ምሬት ከተነሱት ጥያቄ አዘል አስተያየቶች ይጠቀሳል፡፡ የመብራት መቆራረጥና የኢኮኖሚው በደላሎች መዘወር ከተነሱ ሌሎች ጥያቄዎች ናቸው፡፡

ለነዚህ ጥያቄዎች በቅደም ተከተል ምላሽ የሰጡት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ እና የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሶፍያ ካሳ ናቸው፡፡

ከምንዛሬ ፈተና ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የኢንደስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ታረቀኝ፤ “የጥቁር ገበያው ተጽእኖ እና የሚፈጥረውን ልዩነት መታየት ያለበት ነው” ብለዋል፡፡ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሶፍያ ካሳ በፊናቸው ህገወጥ ንግድና ድለላ የኢኮኖሚው ዋነኛ ፈተና መሆኑን በማንሳት በተለይም ዘንድሮ በማዳበሪያ ስርጭት ላይ ያጋጠመውን የ100 ኪ.ግ. ማዳበሪያ ሽያጭ ከ4 ሺህ ወደ 12 ሺኅ ብር ድረስ በማሻቀብ ህገወጦች ያሏቸው እንደሚሸጡ አመልክተዋል፡፡ የንግዱ ማህበረሰብ ይህ አጠቃላይ አገር ላይ የሚፈጥረውን ጫና አገናዝበው የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱም ጠይቀዋል፡፡

Äthiopien Handel und Tourismus vor Herausforderungen | Sitzung Regierung und Privatsektor
ምስል Seyoum Getu/DW

የንግድ ማህበረሰቡን ከመንግስት ጋር ፊትለፊት የሚያገናኘው መሰል መድረክ በተለይም የንግዱ ማህበረሰብ የሚጋፈጧቸውን ፈተናዎች በማቃለል ረገድ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ያሉት ደግሞ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ እና የፓን-አፍሪካ ንግድና ኢንዱስትሪ ም/ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ክቡር ገና ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍን የፈተነው ተግዳሮች እና በኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ላይ ነው የተባለለት የዲጂታል ገበያ እንቅስቃሴ እና ተግዳሮቱም የዚህ መድረክ አቢይ ትኩረት ነበር፡፡

ስዩም ጌቱ

ኂሩት መለሰ

ታምራት ዲንሳ