1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐረር ከተማ እየተረጋጋች ነው?

ዓርብ፣ ጥር 15 2012

በሐረር ከተማ ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት ተሳትፎ የነበራቸውን ሰዎች በቁጥጥር ስር የማዋል ስራውን ገፍቶ እየሰራ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ አስታውቋል። ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ግን መደበኛ ባልሆነ መልኩ በከተማዋ ውስጥ የተደራጁ ወጣቶች አሁንም ስጋት ሆነውብናል ይላሉ። 

https://p.dw.com/p/3Wmdk
Äthiopien Alltag in Harar
ምስል DW/M. Gerth-Niculescu

ሐረር፦አኹንም ስጋት አለ (ነዋሪዎች)

የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ በዋዜማው እና በበዓሉ ዕለት በሐረር ከተማ የሰው ሕይወት ከጠፋበት እና ንብረት ከወደመበት በኋላ ከተማዋ አሁን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ እየተመለሰች መሆኗን የከተማዋ አስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ አስታውቋል።  አስተያየታቸውን ለዶይቸ ቬለ የሰጡ አንድ የከተማዋ ነዋሪ ደግሞ በከተማዋ የሚታዩ መደበኛ ያልሆኑ የወጣቶች አደረጃጀቶች አሁንም ለነዋሪው ስጋት ናቸው በማለት ገልጸዋል።

በሐረር ከተማ በጥምቀት በዓል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የሁለት ሰዎች ጠፍቷል ፣ በርከት ያሉ ሰዎች ቆስለዋል፤ ስድስት ህንጻዎች የመሰባበር እና በአንዱ ላይ የቃጠሎ ጉዳት እንዲሁም ለጊዜው ግምቱ ያልታወቀ ንብረት ተዘርፏል ፣ ተቃጥሏል አልያም ተሰባብረዋል በማለት የሐረሪ ክልል አስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ናስር ዩያ ይናገራሉ።

በከተማዋ ተፈጥሮ በነበረው እና ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጥፋት ላይ ተሳትፎ ነበሯቸው ያሏቸውን 59 ሰዎች በህግ ቁጥጥር ስር ማዋላቸውንም ነው አቶ ናስር ዩያ የገለጹት። በሐረር ከተማ ተፈጥሮ በነበረው በዚሁ ግጭት በንግድ ድርጅታቸው ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ የተፈጸመውን የጥፋት ልክ እንኳ ማወቅ እንዳይችሉ መታገዳቸውን በከተማዋ በንግድ ስራ የተሰማሩ ባለ ሃብት ይናገራሉ። ንብረታቸውን ከጥፋት መከላከል ያልቻለ የመንግስት ጦር ችግሩ ካለፈ በኋላ ጉዳት የደረሰበትን ድርጅታቸውን ማየት እንዳልችል ተከልክያለሁ በማለት ይገልጻሉ።
በሐረር ከተማ በኃይማኖትም ይሁን በብሄር ስም ግጭቶች እንዲፈጠሩ በማድረግ ከተማዋ ለዘረፋ እና የእርስ በእርስ ግጭት እንድትጋለጥ እያደረገ ያለ በወጣቶች ስም የተፈጠረ መደበኛ ያልሆነ አደረጃጀት የከተማዋን አስተዳደር አቅም አሳጥቶ ለነዋሪዎቹም ስጋት ሆኗል የሚሉት ደግሞ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሐረር ከተማ ነዋሪ ናቸው።

በእርግጥ እንደተባለው የሐረር ከተማ በወጣቶች ስም በተዋቀሩ መደበኛ ያልሆኑ አደረጃጀቶች ስጋት ውስጥ ናት ወይ? በማለት ዶይቸ ቬለ የከተማዋን የአስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ናስር ዩያን ጠይቋል። እንደ እርሳቸው መደበኛ ያልሆነ የተባለው የአደረጃጀት ሰንሰለቱ ከድሬ ዳዋ እስከ ጂጅጋ የተዘረጋ ስለመሆኑ ይናገራሉ ። የከተማዋ አስተዳደር በውስጡ ያለውን ይህንኑ ስጋት ሆኗል የተባለውን ኃይል እየተቆጣጠሩ ከሌሎች ስፍራዎች የሚመጡትን ደግሞ ከየአካባቢዎቹ አስተዳደሮች ጋር ተቀናጅተው በመስራት ለመቆጣጠር እየጣሩ መሆኑን ያክላሉ።

በከተማዋ የተፈጠረውን የንብረት ውድመት በተመለከተም ዝርዝር ጥፋት ምን እንደሆነ ተጣርቶ አለመጠናቀቁን አቶ ናስር ተናግረዋል። 
የምስራቅ ኢትዮጵያ የጸጥታው ስጋት ፣ ስጋት ሆኖ ስለመቀጠሉ ግን ረቡዕ ምሽት በሀሮማያ ከተማ ባልታወቁ ሰዎች ተፈጸመ በተባለ ጥፋት አንድ ተሽከርካሪ መቃጠሉን ዛሬ ከሐረር ወደ ድሬዳዋ እየተጓዙ ሳለ ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው አንድ የሐረር ከተማ ነዋሪ በአይናቸው ያዩትን ይናገራሉ።

ሁኔታዎችን እየጠበቀ የሚያገረሸው የትልልቆቹ የምስራቅ ኢትዮጵያ ከተሞች ችግር እንደተባለው በፍጥነት ተቀርፎ ሰላም ይሰፍን ይሆን?  ወይስ የነዋሪው ስጋት ስጋት እንደሆነ ይቀጥል ይሆን?

Hyänen Äthiopien
ምስል Reuters/T.Negeri

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ