1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተሳታፊዎች ልየታ በአዳማ

ሐሙስ፣ የካቲት 14 2016

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሀገራዊ መግባባት ውይይቱ ላይ የሚሳተፉ ተሳታፊዎች ልየታ ማድረጉን ቀጥሏል። ኮሚሽኑ ትናንት በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ የወረዳዎች የማኅበረሰብ ተወካዮች ልየታ ባከናወነበት ወቅት በክልሉ ሦስት አራተኛውን ያህል ሥራ ማጠናቀቁን አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/4ckDl
Äthiopien Oromia 2024 | Teilnehmer für Diskussionen der Ethiopian National Dialogue Commission NDG
ምስል Seyoum Getu/DW

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተሳታፊዎች ልየታ ሥራ

ቀሪው የልየታ ሥራ ግን በጸጥታ ችግር ምክንያት መስተጓጎሉን በማመልከትም ኮሚሽኑ በቀጣይ እነዚያ አካባቢዎችም  በምክሩ እንዲሳተፉ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር እንደሚሠራ ጠቁሟል። በአብዛኛ ክልሎች የልየታ ሥራው መጠናቀቁንም በማንሳት፤ በትግራይ እና አማራ ክልሎች ግን የነበረው የጸጥታ ሁኔታ ሥራውን ቢያጓትትም፤ አሁን አስቻ ሁኔታ እየተፈጠረ በመሆኑ የተሳታፊዎች የልየታ ሥራውን ለማድረግ ዝግጅት ተጠናቋል ነው የተባለው፡፡

የተሳታፊዎች ልየታ እና ከተሳታፊዎች የሚጠበቀው

ትናንት ኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ውስጥ ከምሥራቅ ሸዋ ዞን ከተለያዩ ወረዳዎች የተለያዩ የማኅበረሰብ አካላትን የወከሉ የተባሉ ተሳታፊዎች በተገኙበት ስለ ኮሚሽኑ እና ሂደቶቹ ገለጻ ከተደረገ በኋላ በሀገራዊ ምክክሩ በቀጥታ የሚሳተፉት የማኅበረሰብ ተወካዮች ልየታ ተከናውኗል። በልየታው ከየወረዳው ተወክለው የተገኙትም ተሳታፊዎች የወከሉዋቸውን ማኅበረሰብ ወክለው በተሳትፏቸው ሂደት ሰላምና መግባባት እንዲሰፍን እንደሚጥሩ ገልጸዋል።

ዘገየ አስፋው በአጋራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር
ዘገየ አስፋው በአጋራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምስል Seyoum Getu/DW

11 የኮሚሽነሮች አባላት ያሉት የኮሚሽኑ አንዱ አባል የሆኑት አቶ ዘገዬ አስፋው ከተመሰረተ ለሁለት ዓመታት እየተግደረደረ ባለው በዚህ ኮሚሽን በትልቅ ትኩረት የተሠራው የተሳታፊዎች ልየታ ነው ብለዋል። «ከትግራይ እና አማራ እንዲሁም አንድ አራተኛው ያህል የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ካልሆነ በቀሪው የሀገሪቱ ክፍሎች የልየታ ሥራው ተጠናቋል።» ያሉት ኮሚሽነሩ።

 

በተያዘው ኣመት የኮሚሽኑ ውጥን

ኮሚሽነሩ እንዳሉት በተያዘው ዓመት በመላው ሀገሪቱ የተሳታፊዎች ልየታን በማጠናቀቅ ወደ የምክክር አጀንዳ አሰጣጥ ይገባል። ለዚህም ደግሞ ህዝቡ በትክክልም ይወክለኛል ያለውን ተሳታፊ እየወከለ እንደሚሆን ነው የተገለጸው። ኮሚሽነሩ፤ ይህን ሲገልጹም፤ «ህዝቡ ትክክለኛ ወኪሉን ስለሚያውቅ አጀንዳውን የሚያነሳለትን ሰው በቀጥታ እየመረጠው» መሆኑንም አመልክተዋል።

አምባዬ ዉጋቶ  በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር
አምባዬ ዉጋቶ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምስል Seyoum Getu/DW

በኮሚሽኑ ላይ ስለሚነሳው የገለልተኝነትና አካታችነት ጥያቄ በኮሚሽኑ ዓይን

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከሁለት ዓመታት ገደማ በፊት ሲመሰረት የኮሚሽኑን አካታችነትና ገለልተኝነት አጠያያቂ በማድረግ ሂደቱን ተቃውመው እራሳቸውን ያገለሉ የፖለቲካ ድርጅቶ አሁንም ድረስ አሉ። እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች እራሳቸውን የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች «ካውከስ» በሚል እራሳቸውን ለይተው በኮሚሽኑ ላይ ጥያቄ ማንሳታቸውንም ቀጥለዋል። ስለዚሁ ጉዳይ እና እልባቱን አስመልክቶ ከዶቼ ቬለ ጥያቄ የቀረበላቸው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አባል ኮሚሽነር አምባዬ ውጋቶ፤ ኮሚሽናቸው ሁሉንም በገለልተኝነትና አካታችነት የሚያገለግለው በመርህና ሕግ ጭምር ተደግፎ ነው ብለዋል። «የተለየ ሃሳብ ያለው ማንም ኢትዮጵያዊ፤ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላትም ጭምር በውይይቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ እንፈልጋለን» ነው ያሉት። ይህንኑን ተቀራርቦ አብሮ በመሥራት ብቻ እንደሚረጋገጥም ጠቁመዋል።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ