1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እልባት የሚሹት የእገታ ወንጀሎች ነዋሪዉን እያማረሩ መሆኑ

ሰኞ፣ ኅዳር 3 2016

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን እየተባባሰ የመጣዉ የእገታ ወንጀል እንዳማረራቸው ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ በአርሲ ዞን ሰዎችን አግቶ ከፍተኛ መጠን ያለዉ ገንዘብን የመጠየቅ ህብረተሰቡን አማሯል ብለዋል፡፡ የዞኑ ፖሊስ በበኩሉ ጉዳዩ አልፎ አልፎ በደናማ አከባቢዎች መሰል ተግባር ቢታይም፤ የመኪና መንገድ እና ከተሞች ዙሪያ ይህ ተግባር አይሰማም ብሏል።

https://p.dw.com/p/4YkOs
ኦሮምያ ክልል አርሲ ዞን የሚገኙመኖርያ ቤቶች
ኦሮምያ ክልል አርሲ ዞን የሚገኙመኖርያ ቤቶችምስል Fischer/Bildagentur-online/picture alliance

ስጋቱ እያየለ የመጠዉ የእገታ ወንጀል በኦሮምያ

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን እየተባባሰ የመጣዉ  የእገታ ወንጀል እንዳማረራቸው ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ፡፡ በአርሲ ዞን አሰላ ከተማ ዙሪያ ነዋሪ የሆኑ አስተያየት ሰጭዎች ሰዎችን አግቶ ከፍተኛ መጠን ያለዉ ገንዘብን የመጠየቅ ተግባር ህብረተሰቡን አማሯል ብለዋል፡፡ የዞኑ ፖሊስ በበኩሉ በዞኖ ውስጥ አልፎ አልፎ በደናማ አከባቢዎች መሰል ተግባር ሲፈጸም ቢታይም፤ የመኪና መንገድ አስፋልት ላይ እና ከተሞች ዙሪያ ይህ ተግባር አይሰማም፤ ፍጹም ሰላማዊ እንቅስቃሴ ነዉ የሚስተዋለዉ ሲል ገልጿል።

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀው አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪ በአርሲ ዞን ከአሰላ ከተማም በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኙ ገጠራማ ቀበሌያት፤ በተለይም ቂሊሳ በሚባል አከባቢ በሌሊት ሰዎችን በማገት ገንዘብ መጠየቅ እየተለመደ የመጣ ተግባር ሆኗል ነው የሚሉት፡፡

እንደነዋሪዎች አስተያየት ከከተማ ውጪ ያለው የትኛውም አከባቢ መሰል ስጋት አለ፡፡ “በተለይም በተጨባጭነት የማውቀው ሄጦሳ ወረዳ ቂሊሳ በሚባል ቦታ መሰል የእገታ ተግባር በጣም በተደጋጋሚ ተፈጽሟል፡፡ ይህ ቦታ ቁሉምሳ ከሚባለው የአሰላ ከተማ መግቢያ አከባቢ እጅግ ቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ነው” ብለዋል፡፡ አስተያየት ሰጪው ሰዎች  ሲታገቱ ባላቸው የኢኮኖሚ አቅም የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ እንዲከፍሉ በአጋቾቻው እንደ ሚወሰንባቸው ያስረዳሉ፡፡ የታገቱት ሰዎችም የተጠየቁትን ተደራድረው ከፍለው ከመውጣት ውጪ ህይወታቸውን የማቆያ ሌላ ስልት እንደሌላቸው ነው የሚያስረዱት፡፡ኢትዮጵያ ዉስጥ የታገቱት ሰዎችና አጋቾች

ዶይቼ ቬለ እገታውን በውል ማን እንደሚፈጽም ነዋሪዎች የሚያውቁት ይኖር ይሆን በሚል ጥያቄ ያቀረበላቸው አስተያየት ሰጪው አረ በፍጹም የሚል ምላሽ ነው የሰጡት፡፡ “ያው ማን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ እሱም አይደል ትልቁ ችግር” በማት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አስተያየት ሰጪው ከፍተኛ የአርሶ አደር የኢኮኖሚ አቅም የሚስተዋልበት አከባቢው በቀጣይም ለመሰል ዘረፋ ተጋላጭ እንዳኆን በማለት ስጋታቸውን አጋርተውናል፡፡ በአከባቢው ነዋሪዎች የሰቀቀን ህይወት እየመሩ ነው የሚሌት አስተያየት ሰጪው፤ “ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው አርሶ አደሮች አከባቢውን ለቀው ወደ ከተማ በመሸሽ ላይ ሲሆን አቅም የሌለው ግን አከባቢው ላይ ተቀምጦ የሰቀቀን ህይወት መራል” ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡

ሌላው ስሜ አይጠቀስ ብለው ድምጻቸውንም እንዳንጠቀም የጠየቁን የዶዶታ ወረዳ ነዋሪ አጎታቸውን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ከአከባቢው ያለ ምንም ጥፋት በሌሊት ታግተው ገንዘብ ከፍለው ወጥተዋል ብለዋል፡፡ መሰል የጸጥታ ስጋት አልፎ አልፎ ጋብ ሲል አንዳንዴ ደግሞ ደጋግሞ እንደሚከሰትም በአስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኦሮምያ ክልል ወንጪ ባህር
ኦሮምያ ክልል ወንጪ ባህርምስል Seyoum Getu/DW

መሰል ነዋሪዎችን በማገት ገንዘብ የመጠየቁን የእገታ ስራ በዞኑ እንደሚፈጸም የዞኑ መንግስት አስተዳደርም ያውቃል፡፡ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡት የአርሲ ዞን ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ኮማንደር አህመድ ከድር ለዶይቼ ቬለ እንደነገሩት፤ ችግሩ ጎልቶ የሚስተዋለው ከከተማ ራቅ ባሉ ደናማ አከባቢዎች ነው፡፡ “እንደሚባለውም ሳይሆን አልፎ አልፎ በአንዳንድ አከባቢዎች በደን በተሸፈኑ ገጠራማ አከባቢዎች በተለይም ወደ አኖሌ ባሉ ደናማ የዝዋይ ዱግዳ ወረዳ አዋሳኝ ነው ይህን መሰል የእገታ ተግባራት የሚፈጸሙት፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ተግባሩን ለማስቆም የሚወሰዱ ኦፕሬሽኖች በመኖራቸው እንዲህ ጎልቶ በከተማ ዙሪያ የሚፈጸም ነገር የለም፡፡ በተለይም በአሰላ ከተማ ዙሪያም ሆነ በአስፓልት መንገዶች ላይ እንዲህ ያለ ነገር የለም፡፡ ወንጀሉ አልፎ አልፎ የሚስተዋለው በዶዶታ እና ሁሩታ ወረዳዎች ዳገታማ አከባቢዎች እና ከምስራቅ ሸዋ ዝዋይ ዱግዳ ጋር ከሚያዋስኑን አከባቢ ነው፡፡”

የአርሲ ዞን ፖሊስ መመሪያ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊውን ኮማንደር አህመድን መሰል ወንጀል የሚፈጽመውስ ማነው የሚል ጥያቄም አቅርበንላቸው፤ “መሰል ተግባርን የሚፈጽሙ በውንብድና ስራ የተሰማሩ አሉ፡፡ አንዳዴ ኦነግ ሸነ በሚል ትጥቅ አንግቦ በጫካ የሚንቀሳቀሰውን ሃይል እንደ ሽፋን በመጠቀም በዝርፊያው የተሰማሩ መኖራቸውን አረጋግጠናል፡፡ በዝርፊያ ላይ እያሉም ጭምር ተቆጣጥረን ለህግ ያቀረብናቸው አሉ” ብለዋል፡፡ስጋቱ እያየለ የመጣው እገታ በኦሮሚያ ክልል

ከዚህ አኳያ ምን ያህል ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ለህግ ቀርበው ይሆን ለሚለው ጥያቄ ግን ኃላፊው ዝርዝር ምላሽ አልሰጡም፡፡ ይሁንና ፖሊስ ያካሄዳል ባሉት የተለያዩ የኦፕሬሽን ስራዎች ወንጀሉን የመከላከል ስራ እየተከናወነ ነው ይላሉ፡፡ “እንደ ዞን ፖሊስ በተለያዩ ጊዜያት ኦፕሬሽን እናካሄዳለን፡፡ በዚህ ውስጥ ግንዛቤ በመፍጠር ህብረተሰቡን እናሳትፋለን፡፡ ከታጣቂዎች በተጨማሪ በታጣቂዎች ስም የተደራጁ መኖራቸውንም ህዝቡን እናስገነዝባለን፡፡ እነዚህ ማህበረሰቡን በስልክ ጭምር እየደወሉ የሚያስፈራሩትን ተከታትለን እየያዝን ነው፡፡”

በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ወይም መንግስት ሸነ በሚል በአሸባፈሪነት የፈረጀው ታጣቂ ሸማቂ ቡድን እና የመንግስት ጦር ለዓመታት ባካሄዱት መጠነ ሰፊ ውጊያ የክልሉ ጸጥታ ሁኔታ ክፉኛ መፈተኑ ተደጋግሞ ተነገግሯል፡፡ ውጤቱ በማህበረሰቡ ዘንድ በጉልህ የሚጠበቀው ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ባሁን ወቅት በክልሉ ያለውን የተወሳሰበውን የጸጥታ ሁኔታ ዘላቂ እልባት ለመስጠት ነው በሚል በታንዛንያ ዳረሰላም የተቀመጡት ድርድርም በሂደት ላይ መሆኑ ከመነገሩ ውጪ እስካሁን ውጤቱ በይፋ አልታወቀም፡፡

 

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ