1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኃይል ማመንጨት የጀመረዉ ህዳሴ ግድብና የአካባቢዉ ፀጥታ ሁኔታ

ሰኞ፣ የካቲት 14 2014

በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኙው ኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ሐይል ማመንጨት መጀመሩን ተከትሎ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ደስታቸውን  እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ በክልሉ ለረዥም ጊዜ በቆየው የሰላም ችግር ምክንያት ነዋሪዎች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል፡፡

https://p.dw.com/p/47Lqv
ETHIOPIA-EGYPT-SUDAN-DAM-ELECTRICITY
ምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

«በስፍራው ለሚስተዋለው ጸጥታ ችግር መንግስት ትኩረት አልሰጠም»

 

በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኙው ኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ሐይል ማመንጨት መጀመሩን ተከትሎ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ደስታቸውን  እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ በክልሉ ለረዥም ጊዜ በቆየው የሰላም ችግር ምክንያት ከአሶሳ ከተማ ወደ መተከል ዞን የሚወስደው መንገድም ከተዘጋ አንድ ዓመት ያለፈው ሲሆን ነዋሪዎች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች   ያላቸውን ስጋት ለዲዳቢሊው ተናግረዋል፡፡

የግንባታ ሂዴቱ ከተጀመረ አስራ አንድ ዓመት ያህል የሆነው  የታላቁ ህዳሴ ግድብ  ትናንት የካቲት 13/2014 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት ሐይል የማመንጨት ስራ ጀምሯል፡፡ የግድቡ ስራ መጀመርን ተከትሎ ያነጋርናቸው የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች  ያላቸውን ሀሳብ ገልጸዋል፡፡ በሀገሪቱ በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች ለረዥም ጊዜ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ላልሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ተስፋ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ መገኛ በሆነው መተከል ዞን ውስጥ ለሚስተዋለው የጸጥታ ችግርም መንግስት መፍትሄ ሊያበጅ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ የቦሮ ዶሞክራቲክ ፓርቲ  በበኩሉ በአፍሪካ ትልቁ ፕሮጅክት በሆነው ወደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚወስደው የመንገድ መሠረተ ልማት ደረጃውን የጠበቀ አለመሆን እና በስፍራው ለሚስተዋለው ጸጥታ ችግር መንግስት ትኩረት አልሰጠም ብለዋል፡፡  በተለይም ወደ ግድቡ የሚወስዱ የጉዞ እንቅስቃሴዎች በጸጥታ ሐይሎች እጀባ ብቻ መሆኑ በአካባቢው ያለው የጸጥታ ችግር  ስር የሰደደ መሆኑን አመላካች ነው ሲሉ የፓርቲው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዩሐንስ ተሰማ ለዲዳቢሊው ተናግረዋል፡፡ 

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ትናንት 375 ሜጋ ዋት ሀይል ማመንጨት ጀምሯል፡፡ የግንባታ ሂዴቱ ሲጠናቀቅም 5150 ሜጋዋት የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን የግንባታ አፈጻጸሙ በአሁኑ ጊዜ 84 በመቶ መድረሱ ተገልጸዋል፡፡ ከአሶሳ ከተማ የግድቡ ግንባታ በሚከናወንበት መተከል ዞን ጉባ ወረዳ በኩል ወደ መተከል ዞን ከተማ ግልገል በለስ የሚወስደው መንገድ በጸጥታ ችግር ምክንያት መደበኛ አገልግሎት ከተቋረጠ አንድ ዓመት አልፎታል፡፡ በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም በተሽከርካሪዎች ላይ ይደረስ በነበሩት ጥቃቶች ምክንያት በስፋራው የነበረው አስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር/ኮማንድ ፖስት መንገዱ ሠላም መሆኑ በኮማንድ ፖስቱ እስካልተረጋገጠ ድረስ መንቀሳቀስ እንደማቻል በወቅቱ ገልጾ ነበር፡፡

 

ነጋሳ ደሳለኝ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ