1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ታሊባን ሲነግስ፣ አሜሪካ እብስ

ሰኞ፣ ነሐሴ 10 2013

እንደ ቡሽ ከኩያን የፀዳችዉ፣ እንደ ባይደን ለአፍቃኖች የተተወችዉ አፍቃኒስታን ዛሬ በታሊባን ሙሉ ቁጥጥር ስር ነች።የወደፊት መፃኤ እድሏ ወሳኞችም  ቡሽ፣ ብሌር፣ ኦባማ፣ ትራምፕ ባይደንም አይደሉም።ድፍን ሃያ ዓመት፣ ተሸነፉ፣ ተደመሰሱ፣ ታደኑ፣ ተገደሉ ሲባሉ የነበሩት የታሊባን ሙላሆች ናቸዉ

https://p.dw.com/p/3z3ab
Afghanistan Einmarsch der Taliban in Kabul
ምስል Zabi Karimi/AP Photo/picture alliance

የታሊባን ድል፣ የምዕራባዉያን ሽንፈትና ሽሽት

ፕሬዝደት ጆርጅ ቡሽ ታሊባንን ሊያጠፉ፣ መከላከያ ሚንስትር ዶናልድ ራምስፌልድ የነሙላሕ ዑመር መሐመድን ማንቁርት ሊፈጠርቁ ፎክረዉ፣ ዝተዉ ነበር።ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር  ለታሊባኖች ፍፃሜ፣ ለአፍቃኒስታኖች ዕድገት፣ሠላም ብልፅግና ምለዉ-ተገዝተዉ ነበር።ዛቻ፣ፉከራ፣ቀረርቶዉ በድፍን ዓለም አስተጋብቶ፣ዓለምን ከምዕራባዉያን ጎን ባሰለፈ በሃኛ ዓመቱ ዘንድሮ ታሊባን ሲነግስ፣ የአሽረፍ ጋኒ መንግሥት ሲፈርስ፣ ሃያ ዓመት ያናጠሩ፣ መቶ ሺዎችን የገደሉ-ያስገደሉባት ምዕራባዉያን ጥለዋት አብስ።አፍቃኒስታን ጉደኛ ምድር።የታሊባኖች ድል መነሻ፣ የሃያ ዓመቱ ጦርነት ማጣቃሻ፣የጉደኛዋ ሐገር የወደፊት ጉዞ መድረሻችን ነዉ፤ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

                                      

አፍቃኒስታን የሠፈረዉን ዓለም አቀፍ የፀጥታ ረዳት ኃይል (ISAF) የተሰኘዉ የዓለም ጦር የቀድሞ አዛዥ ብሪታንያዊዉ ጄኔራል ሎርድ ሪቻርድ በቀደም እንዳሉት ምዕራባዉያን መንግስታት አፍቃኒስታን ዉስጥ የከሰከሱት ገንዘብ፣ ያጠፉት ጊዜ ከሁሉም በላይ ያጠፉና የጠፋባቸዉ ሕይወት ብዙ ነዉ።«እኛ-እኛ ስንል ምዕራባዉያን ሐገራት ባጠቃላይ- ዩናይትድ ስቴትስ በተለይ፣ አፍቃኒስታን ዉስጥ የሃያ-ዓመት ጊዜ፣ ገንዘብና ሕይወት አፍስሰናል (ኢንቨስት አድርገናል።)»

Afghanistan Kabul | Menschenmassen am Flughafen in Kabul
ምስል AFP/Getty Images

እርግጥ ነዉ ዩናይትድ ስቴትስ በአሸባሪዎች በተጠቃች መስከረም 2001 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ማግሥት፣ አሸባሪ ያለቻቸዉን የአልቃኢዳ ኃይላት ለማጥፋት አፍቃኒስታን መዝመቷን ያልደገፈ፣ ጦሩን ለማዝመት ያልወሰነ የዓለም መንግሥት አልነበረም።ዘመቻ-ጥቃት ጦርነቱ ባጭር ጊዜ ዉስጥ አሸባሪ ከተባሉት አልፎ የነፃነት ተፋላሚዎችን፣ ወረራ ተቃዋሚዎችን፣ ኃያማኖት አጥባቂዎችን ሁሉ የመደፍለቅ ዝንባሌና ዓላማ መያዙ የፀረ-ሽብር ዘመቻዉን ዓላማና ተልዕኮ አጠያያቂ አድርጎታል።

 

ከዋሽግተንና ለንደን ይንቆረቆር የነበረዉ ፉከራ፣ ስድብና ቀረርቶ ደግሞ እኒያን ለዓላማ የመቆም ፅናት፣የመስዋት ክብር-ጀግንነትን የሚናፍቁ ሸማቂዎችን እልሕ ዉስጥ ከትቶ ቁጥራቸዉን አበራክቶ በየጫካ-ሸለቆዉ እንዲከቱ ሰበብ-ምክንያት ሆኗል።የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚንስትር ዶናልድ ራምስፌልድን የመሳሰሉ እብሪተኞች ያስተላልፉት የነበረዉ መልዕክት ታሊባንን አይደለም ሌላዉን የአፍቃኒስታን ዜጋንም ወደ ዱር የሚጠራ ነበር።ገና ዉጊያዉ እንደተጀመረ ጥቅምት 7፣ 2001 «የገቡበት ገብተን» አሉ ራምስፌልድ ጥቅምት።

 

«ከምንፈልገዉ ዉጤት ለመድረስ፣ የታሊባንን የአየር መቃወሚያና ተዋጊ አዉሮፕላኖችን መጥፋት አለብን።ይደርሳል ተብሎ የሚጠረጠርና የማይጠረጠር የአሸባሪ ጥቃትን በየስፍራዉ መከላከል አይቻልም።ብቸኛዉ መንገድ ጦርነቱን እነሱ ያሉበት ሥፍራ መዉሰድ፣ከየተሸሸጉበት ማዉጣትና ማጥፋት ነዉ»አለቃቸዉም አረጋገጡ።ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ።የድል ዜና አበሰሩም።ሚዚያ 2002።«ታሊባንን ስንደመሰስ የወታደሮቻችን ተልዕኮ ማስገበር አይደለም።(አፍቃኒስታንን) ነፃ ማዉጣት እንጂ።ተሳክቶላቸዋል።የአሜሪካ ጦርም በዚሕ ይኮራል።የአፍቃኒስታኑ ዉጊያ ገና አልተጠናቀቀም።አሜሪካና የተባባሪዎቿ ሐገራት ጦር ባሁኑ ወቅት የተራራ-መስመር የተባለዉን ዘመቻ ከፍተዋል።የአልቃኢዳና የታሊባን ኃይላትን እያደኑ፣እያሳደዱ ነዉ።»

 

የራምስፌልድን ፉከራ፣የቡሽን የድል ተስፋ ከግብ ለማድረስ ዓለም አፍቃኒስታን ላይ ሲራኮት የዋሽግተን-ለንደን መሪዎች ኢራቅ ላይ አዲስ የዉጊያ ግንባር ከፈቱ።ወትሮም ታሊባኖችን ያጠናከረዉ የጅምላ ዉጊያ ጦርነት፣ጊዜዉን ያልጠበቀ፣ በተጭበረበረ መረጃ የተቀነባበረ፣ የዓለምን ሕግ፣የሕዝብን ጥያቄና ተቃዉሞ ንቆ-በጦር ኃይል ጡንቻ የታብየዉ የኢራቅ ወረራ ለታሊባኖችና ለጥቂት ተባባሪዎቻቸዉ መጠናከር ጥሩ መደላድል ነበር የሆነዉ።

ብዙ ቁጥር ለቅፅበት እናስላ።የዩናይትድ ስቴትስ ጦር አፍቃኒስታንን ከወረረበት ከመስከረም 2001 ጀምሮ ከ2 መቶ ሺሕ እስከ 6 መቶ ሺሕ የሚገመት የዉጪና የአፍቃኒስታን መንግስት ወታደሮች ከታሊባንና ከተባባሪዎቹ ጋር ተዋግተዋል።ከ3  ሺሕ በላይ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት አባል ሐገራት ወታደሮች፣ከ4ሺሕ በላይ የኮንትራት ሠራተኞች፣ ከ66 ሺሕ የሚበልጡ የአፍቃኒስታን መንግስት ወታደሮች ተገድለዋል።

Afghanistan | Taliban in Kabul
ምስል REUTERS

50 ሺሕ የታሊባን፣ 2 ሺሕ የአልቃኢዳ፣ 3 ሺሕ የእስላማዊ መንግስት ተዋጊዎች ተገድለዋል።60ሺሕ ሠላማዊ ሰዎች አልቀዋል።እስከ 7 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ አንድም ተፈናቅሏል አለያም ተሰድዷል።አንዲት ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ከ9መቶ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለጦርነቱ ከስክሳለች።

 

ዩናይይትድ ስቴትስ በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በግንባር ቀደምትነት ተዋግታለች፣ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲሕ ብዙ ጊዜ ተባባሪዎችዋን እያስከተለች፣እያባበለች ከኮሪያ ልሳነ ምድር እስከ ሰርቢያ፣ ከቬትናም እስከ ፋርስ ባሕረ-ሠላጤ ያዉም ሁለቴ ተዋግታለች።ለረጅም ጊዜ ስትዋጋ ግን አፍቃኒስታኑ ጦርነት የመጀመሪያዉ ነዉ።20 ዓመት።

 

ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወዲሕ ከፍተኛ ገንዘብ የከሰከሰችበት ጦርነትም የአፍቃኒስታኑ ጦርነት ነዉ።በ20 ዓመቱ ጦርነት የደረሰዉ የሕይወት፣ የሐብት ንብረት ጥፋትና ኪሳራ ከተገኘዉ ዉጤት ጋር እየተነፃፀረ በሚያነጋግበት ወቅት ዘንድሮ ሚያዚያ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እንደ ሴናተር ያፀደቁትን ወረራ በድል ተጠናቅቋል ብለዉት አረፉ።

                                          

 

የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ መንግስታቸዉ በጦርነት የወደመችዉን አፍቃኒስታንን መልሶ እንደሚገነባ ቃል ገብተዉ ነበር።እንዲያዉም በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት የወደመችዉን አዉሮጳን መልሳ የገነባችዉ ዩናይትድ ስቴትስ አፍቃኒስታንን መልሶ ለመገንባት የጆርጅ ማርሻልን ስልትና ልምድ ስራላይ እያዋለች ነዉ-ብለዉም ነበር።

«ተዋግተን ያሻነፍነዉ እርጉም ጠላት ነዉ።ከእንግዲሕ የምንዋጋዉ እኩይ ጠላት ነዉ።ከነዚ እኩያን ነፃ የሆነችና ለመኖር የምትመች አፍቃኒስታንን ዳግም ለመገንባት የጆርጅ ማርሻልን ምርጥ ልምድ ገቢር እያደረግን ነዉ።»

ሚዚያ 2002።በ19ኛዉ ዓመት ዘንድሮ የቡሽን መንበር የያዙት ጆ ባይደን አፍቃኒስታን የዘመትነዉ ለዳግም ግንባታ አይደለም አሉ።

 

እንደ ቡሽ ከኩያን የፀዳችዉ፣ እንደ ባይደን ለአፍቃኖች የተተወችዉ አፍቃኒስታን ዛሬ በታሊባን ሙሉ ቁጥጥር ስር ነች።የወደፊት መፃኤ እድሏ ወሳኞችም  ቡሽ፣ ብሌር፣ ኦባማ፣ ትራምፕ ባይደንም አይደሉም።ድፍን ሃያ ዓመት፣ ተሸነፉ፣ ተደመሰሱ፣ ታደኑ፣ ተገደሉ ሲባሉ የነበሩት የታሊባን ሙላሆች ናቸዉ።ሙላሕ  አብዱል ጋኒ ባራዳር አንዱ ናቸዉ።ጦራቸዉ ትናንት የካቡልን ቤተ-መንግስትን ሲቆጣጠር እንኳን ደስ አለሕ አሉት።ግን እንዳትታበይ።

                                    

«ለሙስሊሙ የአፍቃኒስታን ሕዝብ፣ በተለይም ለካቡል ዜጎች ለዚሕ ታላቅ ድል በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ።ለሁሉም ሙጃሒዲያን መምከርና ማስገንዘብ የምፈልገዉ ደግሞ በጣም የተለየና ያልጠበቀ ሁኔታ ላይ እንገናኛለን።ይህ የሆነዉ በፈጣሪ ድጋፍና ፈቃድ በመሆኑ እብሪተኛ መሆን የለብምንም።»

የዓለም እንቅስቃሴዎችን መዓለት ወሌት ይከታተላሉ የሚባሉት የለንደን ዋሽግተን  ግዙፍ የስለላ ተቋማት ኢራቅ ጅምላ ጨራሽ ጦር መሳሪያ ታጥቃለች በማለት ያሰራጩት መረጃ የተጭበረበረ መሆኑ ሲጋለጥ ዓለም፣ ስለነዚያ ድርጅቶች በጣሙን ዓለምን ስለሚመሩት ኃያላን መንግስታት መርሕና ዓላማ ቆም ብሎ ሊያጠን በተገባዉ ነበር።

Afghanistan | Mullah Baradar Akhund
ምስል Social Media/REUTERS

የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች፣ የብሪታንያዉ ጄኔራል እንዳሉት፣ በአፍቃኒስታኑ ጦርነት መሸነፋቸዉን ለመደባበቅ «አሸባሪና የአሸባሪ ደጋፊ ከሚሏቸዉ ኃይላት ጋር  ድርድር፣ ዉይይት፣ስምምነት ሲሉ ካቡል ላይ ያቆሙትን መንግስትም ሆነ፣ 20 ዓመት ያደራጁ፣ ከታሊባን ጋር ያዋጉ፣ 144 ቢሊዮን ዶላር ያፈሰሱበትን የካቡል የመንግስት ጦርን የወደፊት ሕልዉና ከቁብ አልቆጠሩትም።ግዙፉ የስለላ ተቋማቸዉም የታሊባን ሙላሆች  በረጅም ፂም፣ በክምር ጥምጣም፣ በሰፊ ጀላቢያቸዊዉ የሸፈኑትን ፅናት፣ጉልበት፣ስልትና ብልሐት መተንበይ አልቻሉም።እኒያ ኪታባቸዉን ከክላሺንኮቭ-ቦምባቸዉን ከግልድማቸዉ ጋር ያሸረጡት ተዋጊዎች በዘጠኝ ቀናት እድሜ ከጉጥ ስርጓጉጡ ወጥተዉ በጌጥ ካሸበረቀዉ ካቡል ቤተ-መንግስት ገቡ።

 

ከ2010 እስከ 2013 የብሪታንያ ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ጄኔራል ሎርድ ሪቻርድ ለደረሰዉ ጥፋት እራሳቸዉንም ተጠያቂ ያደርጋሉ።ግን የምዕራባዉያን የጂኦ-ስትራቴጂ ታላቅ ዉቅደት ይሉታል።የአፍቃኒስታኑን ሽንፈት።«ለምሳሌ፣ የአፍቃኒስታን ዜጋ የሆኑ ተርጓሚዎችን ከአፍቃኒስትን እንዲወጡ ስረዳ፣ ይሕ በእዉነቱ ጥሩ አይደለም።ምክንያቱም ይሕ አፍቃኒስታን ብቻ ሳይሆን፣ ኢራቅ፣ ሊቢያና ሶሪያ ላይም የሆነዉን ሽንፈታችንን ለመሸፋፋንና የትኩረት አቅጣጫን ለማስቀየር የሚደረግ ነዉ።ይሕ ባለፉት 20 ዓመታት የምዕራባዉያን የጂኦ-ስትራቴጂ ዉድቀት ነዉ።ከእንግዲሕ  ይደርሳል ብለን የምንፈራዉ እንዳይደርስ ለመከላከል ለምንና ምን ማድረግ እንዳለብን ማብራሪያ ሊሰጥበት ይገባል።»

 

የዩናይትድ ስቴትስና የተባባሪዎችዋ ሐገራት ወታደሮች አፍቃኒስታንን ለቅቀዉ ሲወጡ የቤት እንስሶቻቸዉን፣ መታሰቢያ ድንጋዮችን፣ የቢራ ማከማቻና ማከፋፈያ ግዙፍ ጋኖችን ሳይቀር እየጫኑ ወስደዋል።

ላለፉት ሃያ ዓመታት ምዕራባዉያኑን ባስተርጓሚነት፣ በፕሮፓጋንዳ አጠናቃሪነት፣በሰላይነት ሲያገለግሉ የነበሩ  የአፍቃኒስታን ዜጎችን ግን ከጥቂቱ በስተር አብዛኞቹን አገልግሎቱን እንዳበቃ ዉዳቂ ጥለዋቸዉ ነዉ-የወጡት።በሰብአዊ መብት ድርጅቶች ጩኸት፣ አቤቱታና በመገናኛ ዘዴዎች ትችት፣ከአፍቃኒስታን  እንዲወጡ የተፈቀዳለቸዉም ገና የወረቀቱን ዉጣ ዉረድ ሳጭረሱ ታሊባን ካቡል ላይ ጉብ አለ።

Afghanistan | Taliban in Kabul
ምስል REUTERS

የምዕራባዉያን መንግስታት ኤምባሲዎች ትናንት የዚያችን መከረኛ ከተማ አየር በዶክሜት ቃጠሎ ጢስ ጠለስ ሲያጥኗት፣ ምዕራባዉያንን ሲያገለግሉ የነበሩ የአፍቃኒስታን ተወላጆች በተለይ ወጣቶቹ የምዕራባዉያን ዜጎች የሚያስወጡ አዉሮፕላኖች ላይ እየተጠላጠሉ፣ ባግራም አዉሮፕላን መደንርደሪያ ላይ እየፈረጡ ነዉ።

ፕሬዝደንት አሽረፍ ጋኒ ግን ዘየዱ፣ ለነገሩ ድሮም ሊገዟት ከዉጪ ተመለሱ እንጂ ጭንቋን ብዙ አያዉቁትም።ትናንትም አራቱ የካቡል በሮች በታሊባን ጦር ሲከበብ ጣጠኛዋን ሐገራቸዉን ጥለዉ ዉልቅ።እና ታሊቢን ነገሰ።የአፍቃኒስታን እስላማዊ ኤሚሬት ተመለሰ።

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ