1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለ ኦሮሚያ ክልል አለመረጋገትና እልባቱ የኦነግ መግለጫ

ዓርብ፣ ሰኔ 16 2015

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ለኦሮሚያ የሰላም ችግር መፍትኄው ሰላማዊ ውይይት ነው አሉ ። አቶ ዳውድ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መንግስት ለውይይት መቀመጥ ያለበት የእሳቸው የፖለቲካ ድርጅትን ጨምሮ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ነው ብለዋል ።

https://p.dw.com/p/4SzsU
Dawud Ibsa, Oromo Liberation Front (OLF) Chairman
ምስል Seyoum Getu/DW

«የሰላም ችግር መፍትኄው ሰላማዊ ውይይት ነው»

በጎርጎሪዮሱ 1973 ሐምሌ 01 የተመሰረተው ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች በአንጋፋነቱ የሚጠቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) 50ኛ ዓመቱን በአገር ውስጥና በተለያዩ አገራት በድምቀት ለማክበር ማቀዱን ጠቅሰው ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት ሊቀመንበሩ አቶ ዳውድ ኢብሳ፤ በፓርቲው የትግል ሂደት ውስጥ የተሰው ጓዶቻቸውን አስታውሰው አመስግነውአቸዋል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘው ስለወቅታዊ አገራዊ ፖለቲካ እና የፓርቲያቸው ይዞታ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ዳውድ፤ ለአሁናዊው በተለይም የኦሮሚያ አለመረጋጋት መነሻ ያሉትንም ሃሳብ አስቀምጠዋል፡፡   

“በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኢትዮጵያ መንግስት መካከል በጎርጎሳውያኑ ነሐሴ 07 ቀን፣ 2018 ሰምምነት ተደርሶ ነበር፡፡ በዚህ ስምምነት መሰረት ጦርነት ቆሞ ኦነግ በህዝቡ መሃል ሆኖ በነጻነት የፖለቲካ እንቅስቃሴውን እንዲያከናውን፤ ለዚህም ሙሉ መብት አለው የሚል ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ ለኦሮሞ ነጻነት ግንባር ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ተመሳሳይ ነገር እንደሚፈቅድ ነው የተስማማው፡፡ የስምምነታችን አስኳሉ ይህ ነው፡፡ ከዚህ ጋር የተያያዙ የሰራዊታችን እና ሰላም ጉዳይም በስምምነቱ ውስጥ ነበር፡፡ አሁን ይህ መከዳቱ ነው ላለፉት አምስት ዓመታት በኦሮሚያ የቀጠለውን ጦርነት ያስከተለው፡፡ ለትግራይ ጦርነት እና አሁን በአማራ ክልል እየተስፋፋ ላለውም ቀውስ መሰረት የሆነው፡፡”

ስምምነቱን ተግዳሮት መግጠሙን ተከትሎ ፓርቲያቸው ላይ ከፍተኛ ወከባ መድረሱንም ያነሱት አቶ ዳውድ፤ በኦሮሚያ ዘላቂ ሰላም እንድሰፍን ይበጃል ያሉትንም ሃሳብ ሲጠቁሙ፤ “ይህንን ስምምነታችንን በመሻር ነው እንግዲህ መንግስት በደቡብ እና ምዕራብ እንዲሁም በመሃከለኛው አከባቢ ያሉ የኦነግ ሰራዊት ላይ ትጥቅ ለማስፈታት በሚል ተኩስ የከፈተው፡፡ ይህን በማድረግ ሂደት ውስጥ ሽማግሌዎችም በመሃል ገብተው፤ የቴክኒክ ኮሚቴ በሚባልም ጥረቶች ሲደረጉ የነበረው፡፡ ያም አልሆነም ጦርነቱ ቀጠለ፡፡ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ይህን ሰራዊት አጠፋዋለው በሚል በተደጋጋሚ መግለጫ ሲያወጣ ነበር፡፡ ያ እንዳልሆነ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ያ ጦርነት ጫካ ብቻ ሳይሆን እዚህ ከተማ ውስጥም የኦነግ ጽ/ቤቶችን በመዝጋትና አመራሮቹን በማሰር የፓርቲውን እንቅስቃሴ በመግታትም ጭምር የተደረገ ነበር፡፡ አሁንም እንደ እኛ እምነት በኦሮሚያ ሰላም የሚሰፍነው መንግስት ከዋናው ባለጉዳይ ከእኛ ጋር ተቀምጦ ያ ስምምነታችን ሲከበር ነው ብለን እናምናለን፡፡”

በተለያዩ ጊዜያት የኦነግ አመራሮች ሲታሰሩ መንግስት በሽብርተኝነት ከፈረጀው በኦሮሚያ በስፋት ከሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ጋር ስማቸውን ሲያያይዝ ይደመጣል፡፡ ስለዚሁ ጉዳይ ዶቼ ቬለ ጥያቄ ያቀረበላቸው አቶ ዳውድ ኢብሳ ግን የሰጡት ምላሽ ሌላ ነው ።

“የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር አሁን ላይ ግንኙነት አለው ወይ ለሚለው፤ ያ ሰራዊት የፖለቲካ ጥያቄ ያለው ሰራዊት ነው፡፡ አባላቶቹን ለምን እንደሚታገል አስተምሮ ነው ወደ ጦር የሚያሰማራው፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ደግሞ በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ ይህን ትግል በሰላማዊ መንገድ እያካሄደ ነው፡፡ ይህ መንግስት አለመግባባቱ በተፈጠረ ጊዜ ኦነግን ገመድ ውስጥ አስገብቶ ሁለት ጥያቄዎችን ነው የጠየቀው፡፡ ትጥቅ አልፈታም ያለው ያ ሰራዊት የኔ ነው ወይስ አይደለም እንድንል፡፡ በወቅቱ ከአባገዳዎች ጋር ሆነን በኦሮሞ ባህል ማዕከል ባደረግነው ጉባኤ መንግስት ስምምነቱን አፍርሷል ብለን በማመናችንና ጦሩን ማስገባት ስርዓት ስላለው እኛ በወቅቱ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን ለአባገዳዎች ሰጥተን ነው ከመሃል የወጣነው፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከጦሩ ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ ያን ተከትሎ በምርጫ ቦርድ በሕጋዊ መሰረት ብንንቀሳቀስም ይሄው ቤት ውስጥ እስከመታገት የሚደርስ ጫና ደርሶብናል፡፡ የኦነግ እንቅስቃሴ ግን በተለያየ መንገድ ቀጥሏል እንጂ አይገታም፡፡” 

የኦነግ ባለስልጣኑ በመግለጫቸው ማጠቃለያም “አሁንም የምንጠይቀው መንግስት ሰላም እንዲወርድ ተቀምጦ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ግደታውን ይወጣ” ብለዋል፡፡ አቶ ዳውድ በኦሮሚያ ለሁሉም ዜጋ እኩል ክብር እንዲሰጥና መከባበር እንዲሰፍን ጠይቀዋል፡፡ 

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ