1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መጭው የሴኔጋል ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ

ሐሙስ፣ መጋቢት 12 2016

በመጭው ዕሁድ በጎርጎሪያኑ መጋቢት 24 ቀን 2024ዓ/ም በሴኔጋል ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይካሄዳል። በሳህል ቀጠና የመረጋጋት ምልክት ሆና የቆየችው ሴኔጋል ፤የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል በየካቲት ወር መጀመሪያ ሊካሄድ የነበረውን ምርጫ፤ ቅስቀሳ ሊጀመር ስምንት ሰአታት ብቻ ሲቀሩት ለማራዘም በመወሰናቸው የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ገብታለች ቆይታለች።

https://p.dw.com/p/4dzHq
የሴኔጋል የ2024 የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ
የሴኔጋል የ2024 የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ምስል SEYLLOU/AFP

የ2024 የሴኔጋል ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ


ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ሴኔጋል በመጭው ዕሁድ በጎርጎሪያኑ መጋቢት 24 ቀን 2024ዓ/ም ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ታካሂዳለች።ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በዚህ አመት መጀመሪያ በየካቲት ወር ሊካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ ከታቀደው ጊዜ በመዘግየቱ ለፕሬዚዳንትነት የቀረቡት ዕጩዎች የተሰጣቸው  ጊዜ ከመደበኛው የቅስቀሳ  ጊዜ ያነሰ ነው። በምርጫው 19 እጩዎች የሚወዳደሩ ሲሆን፤ከ7 ሚሊዮን በላይ  መራጮችን ለመቀስቀስ  ሁለት ሳምንት ብቻ ነበራቸው። ከምርጫው ግንባር ቀደም ተፎካካሪ አንዱ የሆኑት ባሲሩ ዲዮማዬ ፋዬ ግን ያላቸው ጊዜ ከዚህም ያነሰ ነው። ምክንያቱም እሳቸው ከሚያዚያ 2023 ጀምሮ በእስር  የቆዩ ሲሆን፤ያለፈው ሐሙስ ነበር  በይቅርታ የተለቀቁት።እናም ከመራጮች ጋር በአካል ለመገናኘት ስምንት ቀናት ብቻ ተሰጥቷቸዋል።

አማዱ ባ - በማኪ ሳል የተመረጡ ተተኪ
ሌላው ዕጩ ተወዳዳሪ በፕሬዚዳንት ማኪ ሳል በእጩነት የተመረጡት አማዱ ባ ሲሆኑ፣ማኪ ሳል ለሦስተኛ ዘመነ ስልጣን አልወዳደርም አሉ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታቸውን ትተው ፕሬዝዳንትነት ለመሆን ቅስቀሳ ጀምረዋልል። የ62 አመቱ አዛውንት በሲቪል ሰርቪስ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላቸው እና የቀድሞው ኢኮኖሚ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሆኑ «የጋራ የብልጽግና » በሚል መሪ ቃል ይፎካከራሉ።

የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል እና በእሳቸው ለመተካት የመረጧቸው አማዱ ባ
የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል እና በእሳቸው ለመተካት የመረጧቸው አማዱ ባ ምስል SEYLLOU/AFP/Getty Images

የወቅቱ ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል የካቲቱን ምርጫን በድንገት ከመሰረዛቸው በፊት ባ የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ ያሸንፋሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር። ነገር ግን የምርጫውን መራዘም ተከትሎ  በገዢው ቤኖ ቦክ ያካር ጥምረት ላይ  ቁጣ በርትቷል። በሳህል ቀጠና የመረጋጋት ምልክት ሆና የቆየችው ሴኔጋል ፤የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል የምርጫ ቅስቀሳ ሊጀመር ስምንት ሰአታት ብቻ  ሲቀሩት ለማራዘም በመወሰናቸው የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ገብታለች። ከዚህ አንፃር የምርጫ ተንታኝ እና ፣በሴኔጋል የምርጫ ግልፅነት የሲቪል ማህበረሰብ ተዋናዮች መድረክ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዲጂብሪል ጂኒንጌ፣  ፈታኙ ነገር የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን ማክበር ነው።ይላሉ።የሴኔጋል ተቃውሞ የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ይጎዳ ይሆን?

«የፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ፈታኝ ሁኔታ፤ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን የሚያከብር ሰላማዊ፣ ሐቀኛ እና ግልጽ የሆነ የድምጽ አሰጣጥን ማካሄድ ነው።»
በአፍሪካ የማህበራዊ ሳይንስ ጥናትና ምርምር ምክር ቤት ባልደረባ የሆኑት ኤሚ ኒያንግ በበኩላቸው አማዱ  ባ ሀብታም እጩ በመሆናቸው በድህነት ውስጥ ያለውን መራጭ ለማሳመን በጣም ከባድ ስራ እንደሚጠብቃቸው አመልክተዋል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በጋዝ እና በነዳጅ ዘርፍ መጠነ ሰፊ መዋዕለ ንዋይ  የሚደረግባት በሴኔጋል 18 ሚሊዮን ከሚጠጋው የሀገሪቱ ህዝብ ከአምስቱ ሦስቱ ከድህነት ወለል በታች ይኖራል።

ባስሩ ዲማዬ ፌይ ከወራት እስር በኋላ
ሌላው ዕጩ ፌይ የሀገሪቱን የፍትህ ስርዓት የሚተች ፅሁፍ በመለጠፋቸው ፤ችሎት በመዳፈር ፣ ስም በማጥፋት እና የህዝብን ሰላም ሊያደፈርሱ በሚችሉ ተግባራት ተከሰው በሚያዚያ ወር 2023 ዓ/ም ለእስር ተዳርገው ነበር። የ49 አመቱ የግብር ተቆጣጣሪ በታዋቂው እና በህዝብ ዘንድ በሚወደዱት በተቃዋሚው ኦስማን ሶንኮ ድጋፍ እስኪያገኑ ድረስ በአንፃራዊነት ብዙ አይታወቁም ነበር። ሶንኮ  ባለፈው አመት ታስረው  መጋቢት 14 ቀን ከፋዬ ጋር ነው ከዕስር የተለቀቁት።የፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ገዥ ፓርቲ ቁልፍ ተፎካካሪ ሆነው ይታዩ የነበሩት ሶንኮ፤ በቀረበባቸው የስም ማጥፋት ክስ ከምርጫ ተሰርዘዋል። ሰፊ ድጋፍ ማግኘታቸውን ግን ቀጥለዋል። ከእስር በመፈታታቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው በዋና ከተማይቱ ዳካር ጎዳናዎችን በማጥለቅለቅ ደስታቸውን ገልፀዋል። ምንም እንኳ ሶንኮ በዘንድሮው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ባይሳተፉም፤የዘመቻ ቅስስቀሳ ወረቀቶች እሳቸውን እና እሳቸው ድጋፍ የሰጧቸው ባሲሩ ዲዮማዬ ፋዬን ጎን ለጎን በማድረግ «ዲዮማዬ ሶንኮ ነው» የሚል መፈክር ይዘው ይታያሉ።

ምንም እንኳን ኦስማን ሶንኮ ከፕሬዚዳንታዊ  ምርጫ ውድድር  ቢገለሉም በቅስቀሳው ወቅት የእሳቸው ምስል ከዲዮማዬ ፋዬ ጋር ጎን ለጎን ተሰቅሎ ይታያል
ምንም እንኳን ኦስማን ሶንኮ ከፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውድድር ቢገለሉም በቅስቀሳው ወቅት የእሳቸው ምስል ከዲዮማዬ ፋዬ ጋር ጎን ለጎን ተሰቅሎ ይታያልምስል SEYLLOU/AFP

ባሲሩ ዲዮማዬ ፋዬ ሙስናን ለመቅረፍ እና በመንግስት እና በኮርፖሬሽኖች መካከል ከሀይል እና ከማዕድን እስከ ዓሣ ማጥመድ ድረስ ያለውን ውል እንደገና ለመደራደር ቃል ገብተዋል ።በሶንኮ ያለው ድጋፍ ተስፋ ሰጪ ምልክት ነው። ምክንያቱም ሶንኮ በስራ እጦት እና በቀጣይ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በጣም የተበሳጩ የከተማው ወጣቶች በሰፊው ተወዳጅ ናቸው። ከሴኔጋል ህዝብ 60% ያህሉ ከ25 ዓመት ዕድሜ በታች ነው።
የሶንኮ-ፋዬ ጎራ በጥንቃቄ የተደራጀ ነው። ባልተጠበቀ ሁኔታ ከእስር ቤት ከመፈታታቸው በፊትም የምርጫ ዘመቻ አራማጆች ቤት ለቤት ቀስቀሰዋል።ዳካር አቅራቢያ በሚገኘው የፒኪን ኖርድ ኮሙዩኒኬሽን የሴቶች ዘመቻ ሃላፊ የሆኑት ፋቱ ቢንቱ ሳርር እንደሚሉት ቀደም ብሎ ሰፊ የቅስቀሳ ስራ ተሰርቷል። «ከዚህ በፊት አጠቃላይ ማህበረሰቡን ሸፍነናል። አሁን ሰዎች ለመምረጥ እንዲሄዱ ብቻ ነው ማድረግ የሚያስፈልገን።»

 ኦስማን ሶንኮ እና የሚደግፉት ፕሬዚዳንታዊ እጩ ባሲሩ ዲዮማዬ ፋዬ ከእስር ሲፈቱ ደጋፊዎች ደስታቸውን ሲገልፁ
ኦስማን ሶንኮ እና የሚደግፉት ፕሬዚዳንታዊ እጩ ባሲሩ ዲዮማዬ ፋዬ ከእስር ሲፈቱ ደጋፊዎች ደስታቸውን ሲገልፁምስል Zohra Bensemra/REUTERS

ምርጫው አብቸኛ ሴት እጩ  ተወዳዳሪ 
ከ19ኙ እጩዎች መካከል በ2019ኙ ምርጫ  ሁለተኛ የነበሩት የ63 ዓመቱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢድሪሳ ሴክ ፣የ68 ዓመቱ፤ የዳካር የሁለት ጊዜ ከንቲባ ካሊፋ ሳል፣ እና የ40 ዓመቷ ስራ ፈጣሪ አንታ ባባካር ንጎም ይገኙበታል።ንጎም በምርጫው የሚፎካከሩ ብቸኛዋ ሴት ናቸው።
የንጎም የዘመቻ ቅስቀሳ ሀላፊ ፋቱ ሲላ «ስለሴቶች እና ወጣቶች ሳታወራ ስለ ሴኔጋል እድገት መናገር አትችልም። ሴት ብቻ ሳትሆን ወጣት እና የኢንደስትሪ ባለሙያም ነች። በጣም እንኮራለን።»ብለዋል።

የሴኔጋል የመጀመሪያው የረመዳን ምርጫ 
አብዛኛው ህዝቧ የእስልምና ተከታይ በሆነባት ሴኔጋል በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የፆም እና  የፀሎት ወር በሆነው በረመዳን ምርጫ ሲደረግ በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።በሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር ከሚገኘው የሊበርቴ 6 ታላቁ መስጊድ ኢማን ሞክታር ንዲያዬ በምርጫው ቀንም ቢሆን  የተከበረው ወር መከበር አለበት ብለዋል ።

የምርጫ ተንታኝ ኤል ሃድጂ ሳኢዱ ኑሩ ዲያ በበኩላቸው በረመዳን ከፍተኛ ተሳትፎ ማግኘት ፈታኝ እንደሚሆን ያምናሉ። ነገር ግን ጾም እንቅፋት መሆን የለበትም ይላሉ። «የዚህ ምርጫ ተግዳሮት የመራጮች ተሳትፎ ነው። ነገር ግን እያንዳንዱ ሴኔጋላዊ ለሀገሪቱ ልማት እና ለአገሪቱ አስተዳደር የበኩሉን ድርሻ ለማበርከት ፍላጎት ካለው፤ ጾም ምርጫ ለመሄድ  እንቅፋት መሆን የለበትም።» ምክንያቱም ለምንመርጠው ፕሬዝዳንት ተጠያቂ መሆን አለብን።በማለት ገልፀዋል።

ዓለም ለሴኔጋልን ምርጫ ለምን ትኩረት ሰጠ
ሴኔጋል በጎርጎሪያኑ 1960 ዓ/ም ከፈረንሳይ ነፃ ከወጣች ወዲህ መደበኛ ምርጫዎችን አካሂዳለች። ሀገሪቱ እንደ ጎረቤቶቿ ማሊ፣ቡርኪናፋሶ እና ኒጀር ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ያልተካሄደባት ሲሆን፤  በሽብርተኝነት፣በግጭት እና በፀጥታ ችግር በሚናወጠው ቀጠና የመረጋጋት ምልክት ሆና ቆይታለች። 

የምርጫውን መራዘም በመቃወም በተካሄደው ሰልፍ ላይ የደህንነት ባለስልጣናትተቃዋሚዎችን  በአስለቃሽ ጭስ ሲበትኑ
የምርጫውን መራዘም በመቃወም በተካሄደው ሰልፍ ላይ የደህንነት ባለስልጣናትተቃዋሚዎችን በአስለቃሽ ጭስ ሲበትኑምስል John Wessels/AFP

ሆኖም የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል የካቲት 25 ሊካሄድ የታቀደውን ምርጫ ለሌላ ጊዜ ለ ለማራዘም በመወሰናቸው ሴኔጋል ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ገብታለች።ለአፍሪካ በዴሞክራሲ በምሳሌነት ትቀጠስ የነበረችው ሴኔጋል ምን ገጠማት?

የሴኔጋል ከፍተኛ የምርጫ ባለስልጣን የሆነው የሕገ-መንግስት ምክር ቤት ፕሬዚዳንቱ ምርጫውን ወደ ታኅሣሥ ለመግፋት ያደረገጉትን ውሳኔ በመሻር ሚያዚያ ወር ከመገባደዱ በፊት ምርጫው እንዲካሄድ ወስኗል።
በሴኔጋል የምርጫ ግልጽነት የሲቪል ማህበረሰብ ተዋናዮች መድረክ ዋና ዳይሬክተር ለጅብሪል ጂኒንጌ አሁን የሀገራቸው ተግዳሮት «የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን የሚያከብር ሰላማዊ፣ ሐቀኛ እና ግልጽ የሆነ የድምጽ መስጫ» ወደነበረበት መመለስ ነው።

ፀሀይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ